. አብዱ አደም እባላለሁ፣ በካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ሚሌኒዬም ህክምና ኮሌጅ በካንሰር ሃኪምነት እና የህክምና ተማሪዎችን በማስተማር አገለግላለሁ። በሙያዬም በተለያዩ ሃላፊነቶች በመሳተፍ 2010 . ወጥ የሆነ የክሊኒካል ካንሰር ህክምና ስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ላይ ተሳትፌአለሁ። በተመሳሳይ አመትም ካንሰር ሃኪሞችን የስራ ምዘና እና ደረጃ (JEG) አዘጋጅቻለሁ::
በአዲስ አበባ ሁለተኛዉና በነሃሴ 2010 . በተከፈተዉ የቅዱስ ጰሎስ ሚሌንዬም ህክምና ኮሌጅ ካንሰር ክፍል ምንም ካልነበረበት ፈታኝ ተስፋ አስቆራጭ ውጣ ውረዶችን በመቋቋም ስራ እንዲጀምር ከማስቻልም አልፎ የህክምና ክፍሉ ሃላፊ በመሆን በመስራት ላይ እገኛለሁ። በዚህም በርካታ ህመምተኞች ከመረዳታቸውም በላይ በብቸኝነት የካንሰር ህክምና ጫና ይበዛበት የነበረውን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ለማገዝ ተችሏል:: በተጨማሪም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ እየተገነባ ባለውና በሀገራችን በታላቅነቱና በሚሰጣቸው አግልግሎቶች ቀዳሚ በሚሆነው የአጠቃላይ ካንሰር ማዕከል ግንባታ ውስጥ ኮሚቴ በመሆን ለስኬታማነቱ የማይተካ ሙያዊና የዜግነት ግዴታየን መወጣት ላይ እገኛለሁ::

የተወለድኩት ገደራ በተባለች ሰሜን ወሎ ደሴ አከባቢ የምትገኝ የገጠር አካባቢ ሲሆን፤ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በደሴ ከተማ ተከታትያለሁ። የህክምና ትምህርቴን በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ትምህርት ቤት በመከታተል በ 2003 ዓ.ም ከህክምና ትምህርት ቤቱ እና የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር  በወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆን ተመርቄአለሁ።

በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ሚሌንዬም ህክምና ኮሌጅ ለሁለት አመታት በጠቅላላ ሃኪምነት ካገለገልኩ በኋላ የድህረ ምረቃ ትምህርቴን በክሊኒካል ካንሰር ስፔሻላይዜሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በመከታተልና በታህሳስ 2010 ዓ.ም በመመረቅ በትምህርት ዘርፉ ከተመረቁ የመጀመሪያወቹ አምስት ስፔሻሊስት ሀኪሞች ለመሆን በቅቻለሁ። ከህክምና፣ ከአስተዳደራዊ እና ከማስተማር ስራዬ ጎን ለጎንም ባለፉት አመታት የጀመርኩት የህብረተሰብ ጤና ማስተርስ ትምህርት ወደ መገባበደዱ ነዉ። 
በሀገራችን ላይ ስለካንሰር ያለዉን ግንዛቤ ለማስፋትም በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስና ህትመት ሚድያዎች ላይ የህብረተሰብ ትምህርት እየሰጠሁ ቆይቻለሁ። አሁን ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ይሄንን ድረ ገጽ ጨምሮ ባሉኝ የማህበራዊ ሚድያ መተግበሪያዎች፤ ማለትም ፌስቡክ እና ቴሌግራም ቻናል በመጠቀም በካንሰር ዙሪያ ትምህርቶችን በማዘጋጀት ከ 2.3 ሚሊየን በላይ ሰዎች አድርሻለሁ። እነዚህ የኢንተርኔት መተግበሪያዎች ህብረተሰባችንን ከማስተማርም በተጨማሪ ህብረተሰቡ በድምጽና በምስል ጭምር መጠየቅ እና ማማከር የሚችልበትን እድል የፈጠሩ ናችው። በተጨማሪም ካለኝ በጣም የተጣበበ ጊዜ በመቀነስ በሳምንት ሶስት ቀናትን በመመደብ ለህብረተሰቡ በስልክ የማማከር አግልግሎትም እሰጣለሁ። በኢትዮጵያ በካንሰር ህሙማን መጠለያ እና ህክምና ላይ በሚሰራዉም የካንሰር ኬር ኢትዮጵያ ግብረሰናይ ድርጅት በበጎ ፈቃድ አገለግላለሁ።የኢትዮጵያ ሄማቶሎጂ እና ካንሰር ህክምና ሃኪሞች ማህበርም (ESHO) መስራች: አመራር እና ኤዲቶሪያል ቦርድ አባል በመሆን አገለግላለሁ።
በ ካንሰር ላይ የተጠና ጥናትም Adequacy of Pathology Reports of Invasive Breast Cancer from Mastectomy Specimens at Tikur Anbessa Specialized Hospital Oncology Center” (https://europepmc.org/article/med/30084708) በግሎባል ካንሰር ጆርናል ላይ እ.ኤ.አ በ2018 አሳትሜአለሁ። 
ባለትዳር እና የሴት ልጅ አባት ስሆን፣ ከቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተኛል፣ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ማየት እወዳለሁ።