You are currently viewing የካንሰር ህመምና የምግብ እጥረት እንዲሁም መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄወች

የካንሰር ህመምና የምግብ እጥረት እንዲሁም መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄወች

መግቢያ
የምግብ እጥረት በሰውነት ስብጥር፣ ተግባርና የህክምና ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር የኃይል፣ የፕሮቲን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ለሰውነት በሚፈለገው መጠን አለመገኘት ነው፡፡ እንደየካንሰር አይነት፤ የካነሰሩ ደረጃ፤ የሕክምናው ዓይነት፤ የምግብ እጥረት መመዘኛዎች ተለዋዋጭ ቢሆንም 31-87% የሚሆኑት የካንሰር ህመምተኞች የምግብ እጥረት እንደሚጋጥማቸው መረጃወች ያሳያሉ፡፡ የምግብ እጥረት መንስኤዎች በካንሰሩ ምክንያት የሚከሰት የምግብ መቀነስ (ለምሳሌ በጉሮሮ ካንሰር ምክንያት ምግብ ለመዋጥ መቸገር ወይም አለመቻል)፤ ከህክምናው ጋር የተዛመዱ ችግሮች (ለምሳሌ ማቅለሽለሽ፣ማስታወክና የአፍ መቁሰል)፤ ሰውነታችን ለካንሰሩ በሚሰጠው ምላሽ ምክንያት የሚከሰተው የሰውነት መቆጣት (Inflamtory Response) እና ህመምና ይገኙበታል። ህክምና ካልተደረገለት ከካንሰር ጋር በተያያዘ የሚከሰተው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የህይወት ጥራትን (Quality Of Life – QOL) እና የመዳን እድልን ከመቀነሱም በላይ በግለሰብ፣ በህብረተሰብ እና በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ጫና አለው።
እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ ችግር የበለጸጉ ሀገራትን ጨምሮ አብዛሀኛውን ጊዜ ቶሎ ሳይታወቅ ወይም ታውቆም ሳይታከም ይቆያል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ግን ጉዳዩ ትኩረት እያገኘ መጥቶ የተለያዩ መመሪያወች (Guidelines) ተዘጋጅተው እየተተገበሩ ሲሆን የአመጋገብ ግምገማ (Screening)፣ የግለሰባዊ የአመጋገብ ማማከር (Consultation) እና አስፈላጊ ከሆነም የተለያዩ የአመጋገብ ህክምና አይነቶችን (Intervention) ለሁሉም ወይም ተጋላጭ ለሆኑ የካንሰር ህመምተኞች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጽሁፌ አሁን ላይ ያሉ አለም አቀፋዊና ሳይንሳዊ መመሪያዎችን መሠረት በማድረግ ለጤና ባለሙያዎች፣ ለካንሰር ታካሚዎችና ለቤተሰቦቻቸው የተመጣጠነ ምግብን በተመለከተ መረጃወችን ለማስተላለፍ እሞከራለሁ፡፡

የማጣራት (Screeing) እና የአመጋገብ ምርመራ
አስተማማኝነታቸው የተረጋገጡ ሳይንሳዊ መንገዶችን በመጠቀም የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና የአመጋገብ ችግሮችን ለመለየት የሚረዱ የተለያዩ ምርመራወችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከአመጋገብ ግምገማ በተጨማሪም የተመጣጠነ ምግብ አወሳስድን፣ የክብደት ለውጥንና Body Mass Index (BMI)ን መከታተል ያስፈልጋል።

ለሰውነት የሚያስፈልግ ጉልበትና የአመጋገብ መስፈርቶች

የካንሰር ህመምተኞች እንደማንኛውም ጤናማ ሰው ተመሳሳይ የምግብ ፍላጎት (25-30ኪሎካሎሪ / ኪግ / ቀን፤ 1.2-1.5 ግ / ኪግ / ቀን / ፕሮቲን) አላቸው፡፡ የተረጋገጠ እጥረት ከሌለ በስተቀር ከፍተኛ መጠን ያላቸው የቫይታሚኖችና ንጥረ ነገሮችን መውሰድ አይመከሩም።

የአመጋገብ ድጋፍ የሚያስፈልግባቸው ሁኔታዎች
1. ለአንድ ሳምንት ወይም ከዚያ በላይ ምግብ መመገብ አለመቻል ወይም
2. ከ1-2 ሳምንታት በላይ የምግብ ፍላጎታቸው ከ 60% በታች ሲሆን ናቸው፡፡

የአመጋገብ ድጋፍ ዓይነቶችም የሚከተሉትን ያካትታል፤

1. የአመጋገብ ምክር (Feeding Consultation) – መመገብ ለሚችሉ ግን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ወይም ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ የካንሰር ህመምተኞች የሚመከር ነው፡፡
2. የምግብ ቱቦ መጠቀም (Enteral Nutrition) – በአፍ መውሰድ አለመቻል ነገር ግን ጨጓራን ጨምሮ የስርዓተ ምግብ ተግባር እንደተጠበቀ ሲሆን የምንጠቀምበት ዘዴ ነው፡፡
3. የደም ስር ምገባ (Parenteral Nutrition) – በአፍ መመገብ ወይም የምግብ ቱቦን በመጠቀም መመገብ በማይቻልበት ጊዜ የምንጠቀምበት ነው፡፡

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የአመጋገብ ሁኔታን ለማሻሻል አስፈላጊ ነውን?
ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ጥንካሬንና አጠቃላይ የአካል ብቃትን ለማጎልበት የሚረዱ እንደ እርምጃና ኤሮቢክስ ያሉ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ መሆናቸውን ነው፡፡

ዶ.ር አብዱ አደም
በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር

Leave a Reply