You are currently viewing ኮሮና እና ካንሰር
ኮሮና እና ካንሰር

ኮሮና እና ካንሰር

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና (COVID-19) የካንሰር ህመምተኞች ማድረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች

የኮሮና ቫይረስ በአሁኑ ሰአት አለማችንን ክፉኛ እየፈተናት ሲገኝ ይህ ጽሁፍ እስከተዘጋጀበት ሰአት ድረስ (23/3/2020፤ 3፡20PM CAT) በ188 ሀገራት 350,646 ሰወችን በሽታው ሲያጠቃ፤ 15,317 ህይወታቸውን አጥተዋል ፤ 100,362 የሚሆኑቱ ደግሞ ከህመማቸው አገግመዋል፡፡ በቅደም ተከተል ቻይና፡ ጣሊያን፡ ስፔን፡ አሜሪካና ኢራን ደግሞ በወረርሽኙ ክፉኛ የተጠቁ ሀገሮች ናቸው፡፡  በሀገራችን ኢትዮጵያም እስካሁን 11 የተረጋገጡ የCOVID-19 ህመምተኞች ተገኝተዋል፡፡ እልህ አስጨራሽ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም የወደፊቱን አሁን ላይ ሆኖ መተንበይ አሰቸጋሪ ነው፡፡
በመላው ዓለም የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎችም በእንደዚህ አይነቱ አሰቸጋሪ ወቅት የፊት ተሰላፊዎች፤ የሀገራቸውና የወገናቸው አለኝታ በመሆን የራሳቸውን ህይወት ጭምር አሳልፎ እሰከመስጠት የሚደርስ መስዋትነት እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ 
በዚህ ወቅት ታዲያ የካንሰር ታማሚወች መረዳት የሚገባቸውን እውነታዎችና ማድረግ ስለሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ማሳወቅ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  የዛሬው ጽሁፌም በዚህ ላይ ያተኮረ ይሆናል፡፡  ነገር ግን ኮሮና የቅርብ ጊዜ ችግር እንደመሆኑ መጠንና አስተማማኝ የሆኑ መረጃወች እጥረት ስላለ ይህ ጽሁፍ የተዘጋጀው ጥቂት የሚባሉ ሳይንቲስቶችና መመሪዎችን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ  ውድ ተከታታዮቼ ጽሁፌን በዚህ መንፈስ እንድታነቡት ግንዛቤ ለማስያዝ እወዳለሁ፡፡

የካንሰር ህመምተኞች ለኮሮና ወረርሽኝ የበለጠ ተጋላጭ ናቸውን?
ከቻይና የተገኙ የተወሰኑ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የካንሰር ህመምተኞች በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ ከሌሎች ሰወች ጋር ሲነጻጸሩ በ 3.5 እጥፍ የበለጠ ህመሙ የከፋ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የካንሰር ታማሚዎች በኮሮና ቫይረስ የመያዝ እድላቸውና ህመሙም የከፋ የመሆን እድል አለው፡፡

  • ኬሞቴራፒ ወይም የጨረር ህክምና እየወሰዱ ያሉ ህመምተኞች
  • የደምና የንፍፊት ካንሰር ፤ መልቲፕል ማዬሎማ (Leukemia, lymphoma or multiple myeloma) ታማሚዎች
  • ኢሚዩኖቴራፒና (immunotherapy) የተወሰኑ አዳዲስ መድሀኒቶችን (targeted treatments ለምሳሌ protein kinase inhibitors (PKI) እና PARP inhibitors) የሚወስዱ ህመምተኞች
  • ባለፉት 6 ወራት ውስጥ የመቅኔ ንቀለ ተከላ የተደረገላቸው ወይም የሰውነትን መከላከያ አቅም የሚያዳከሙ መድሀኒቶችን በመውሰድ ላይ የሚገኙ ህመምተኞች
  • ከካንሰሩ በጨማሪ ተጓዳኝ ህመሞች (ለምሳሌ የልብ ወይም የሳንባ ችግር) ያለባቸው ታካሚዎች

የካንሰር ህመምተኞች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

የካንሰር ህመምተኞች ለኮሮና ቫይረስ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚከተሉት ጥንቃቄዎች ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የካንሰር ህክምናን ማቆም ስለማይቻል ፤ የጤና ተቋማትም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

  • መረጋጋትና መደረግ የሚገባቸውን ትንቃቄዎች ብቻ ማድረግ
  • መረጃዎችን ሲቀበሉ ከአሳማኝ ምንጮች መሆናቸውን ማረጋገጥ
  • የኮሮና ተጋላጭነትን መቀነስ፡
  • እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና መታጠብ
  • የእጅ ንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘሮችን) በአግባቡ መጠቀም
  • ሰው ከሚበዛባቸው ቦታዎች መራቅና ጠያቂወችን ያለማብዛት
  • አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ቤት መቀመጥ፤ ስራን በቤት ውስጥ ማከናዎን፤ በመንገድ ሲሄዱም ሆነ ሰዎች ጋር ከተቀላቀሉ ደግሞ ከ 2 -5 ሜትር እርቀትን መጠበቅ ያስፈልጋል
  • የኮሮና ምልክቶች (ሳል፤ ትኩሳት፤ ራስምታት) ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር አለመቀላቀል
  • ከሀገር ሀገር የሚደረጉ ጉዞወችን ማቆም ወይም መቀነስ
  • የኮሮና ህመም ምልክቶች ከታዩብን በተቻለ ፍጥነት የህክምና እርዳታ ለማግኘት ወደ ሀኪም ቤት መሄድና በሽታው ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳይሰራጭ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ
  • አላሰፈላጊ የሆኑ የሆስፒታል ጉብኝቶችን ማሰወገድ
  • የካንሰር ህክምናቸውን በተመለከተ ከሚከታተላቸው ሀኪም ጋር ሳይመካከሩ ምንም አይነት ለውጥ አለማደርግ፡፡ ነገር ግን የሆስፒታል ጉብኝትን ወይም የቆይታ ጊዜን የሚያሳጥሩ አማራጮች ካሉ ከሀኪምዎ ጋር ምክክር ያድርጉ፡፡
  • የሆስፒታል ቀጠሮ ካለወት ከተቀጠሩበት ሰዓት ቀድመውም ሆነ ዘግየተው አለመሄድ

የካንሰር ህመምተኞች የፊት መሸፈኛን (ማስክ) ማድረግ አለባቸውን?

እስከ አሁኑ ሰአት ድረስ የካንሰር ህመምተኞች ማስከ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያሳይ መረጃም ሆነ መመሪያ የለም፡፡ ሆኖም የአለም የጤና ድረጅትን (WHO) ሌሎች እንደ የአሜሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (CDC) ያሉ ታላላቅ አለም አቀፍ ድርጅቶች ካንሰርን ጨምሮ ለማንኛውም ህመምተኛና የጤና ባለሙያዎች የሚሆኑ መመሪያዎች ስላላቸው እነዚህን ተገባራዊ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ያደጉትን ሀገራት ጨምሮ እየተፈታተናቸው ያለውን የማስከና ሌሎች ራስን መከላከያ ግብአቶች በመሆኑ፤ የተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ላለባቸው ሰዎች ብቻ መስጠቱ አሁን ላይ ሁሉንም የሚያስማማ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የህመሙን ስርጭት ለመቀነስ ሚደረገውን ጥረት ከማገዙም ባሻገር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ያሉንን እጅግ ውስን የህክምና ግብዐቶች በአግባቡ ለመጠቀም ያስችላል፡፡

ለሌሎችም መልዕክቱን ያጋሩ።
አመሰግናለሁ።

ዶ.ር አብዱ አደም
በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል
የካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር 

This Post Has 2 Comments

  1. Tigist Belay

    Thank you Dr. this cery crucial information we need to consider.

  2. Dr Abdu

    የተከበራችሁ ተከታታዮቼ ማርች 23,2020 ፖስት ባደርኩት ፅሁፍ (ከላይ ያለው) ግልፅ ለማድረግ እንደሞከርኩት በዋናነት በግብአት እጥረት ምክንያት እንደ WHO, CDC ያሉ ድርጅቶችና ጤና ሚኒስቴር የካንሰር ህመምተኞች የአፍ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) መልበስ ግዴታ እንዳላደረጉ ገልጨ ነበር:: ሆኖም ግን ሁላችሁም እንደምትገነዘቡት በኮሮና ወረርሽኝ ዙሪያ ያለን ግንዛቤ በጣም ፈጣን በሚባል ጊዜ ውስጥ እያደገና እየተቀየረ ይገኛል:: ይህን ተከትሎም የህክምና መመሪያዎችና ድንጋጌዎች ቶሎ ቶሎ ይቀየራሉ:: በመሆኑም የወረርሽኙን መጨመር ተከትሎ የእኛን ሀገር ጨምሮ ከላይ የጠቀስኳቸው አለም አቀፍ የጤና ድርጅቶችና የተለያዩ ሀገራት ማስክ መልበስን ጤነኛው ህዝብም እንዲተገብር ወስነዋል:: የካንሰር ህሙማን ደግሞ ማስክ በጣሙን ከሚያስፈልጋቸው ሰወች መካከል ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙ በመሆናቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል::

    አዳዲስ ነገሮች ሲኖሩ እመለሳለሁ

    አመሰግናለሁ

Leave a Reply