You are currently viewing የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ መንገዶች

የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ መንገዶች

የማህጸን በር ካንሰር በተቀናጀ ሁኔታ ከተሰራ፤ በደንብ የተጠኑና አሰተማማኝነታቸው የታወቁ የመከላከያ መንገዶች ያሉት የካንሰር አይነት ነው፡፡ እነዚህን መንገዶች በመጠቀምም ነው ያደጉት ሀገራት የማህጸን በር ካንሰርን ከመጠን በላይ በመቀነስ የእናቶች ሞት ምክንያት ከመሆን ያስወገዱት፡፡
የመከላከያ መንገዶቹንም በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡
       ✍️ቀዳማይ መከላከል (primary prevention) እና
      ✍️ዳግማይ መከላከል (secondary prevention)

      ቀዳማይ መከላከል (Primary Prevention)

ይህ የሚያተኩረው ለማህጸን በር ካንሰር ዋነኛ መንስኤ የሆነውን HPV (Human Papilloma Virus) ሁማን ፓፒሎማ ቫይረስን በመከላከል ሲሆን በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ሊተገበር ይችላል፡፡
1.ይህ ቫይረስ በግብረ ስጋ ግንኙነት እንደመተላለፉ መጠን የባህርይ ለውጥ ማምጣት አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ በአፍላ እድሜ ከሚደረግ ወሲብ መቆጠብ፤ ኮንዶምን በአግባቡና ሁሌም መጠቀም፤ ብዙ የወሲብ ጓደኛ ከመያዝ መቆጠብና መሳሰሉት ናቸው፡፡
2.ሌላኛውና ዋናው መከላከያ ደግሞ የ HPV ክትባት ነው፡፡ ይህ ክትባት ለማህጸን በር ካንሰር በዋናነት የሚጠቀሱትን HPV 16 እና 18 ያካተተ ሲሆን ክትባቱ ከተሰጠ በኋላ ሰውነታችን ለነዚህ ቫይረሶች መከላከያ (Antibody) በቅድሚያ እንዲያዘጋጅ ስለሚረዳው ኢንፌክክሽን ሲያጋጥም በቀላሉ ለማስወገድና ካንሰርን ለማካላከል ያስችላል፡፡ ይህ ክትባት ባደጉት ሀገራት ከረጅም አመታት ጀምሮ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን በሀገራችን ኢትዮጵያም ከ December 1, 2018 (እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ ዘመን አቆጣጠር) ጀምሮ እድሚያቸው 14 አመት ለሆናቸው ልጃገረዶች በመሰጠት ላይ ነው፡፡ የክትባቱን ውድነት ከግምት ውስጥ ስናስገባ ይህ እጅግ ይበል የሚያሰኝ ጅምር ቢሆንም ተደራሽነቱን ማስፋፋትና የእድሜ ገደቡንም በአለም አቀፉ የጤና ድርጅትና በሌሎቸም መመሪያ መሰረት እድሜያቸው ከዘጠኝ እስከ 25 አመት ያላቸው ሴቶችን ለማካማተት መሰራት አለበት፡፡

    ዳግማይ መከላከል (Secondary Prevention)

የማህጸን በር ክንሰርን ተፈጥሮአዊ ታሪክ ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ቅድመ ካንሰር ከረጅም ጊዜያት በኋላ ወደ ካሰርነት ስለሚቀየር፤ ይህኛው የመከላከያ መንገድ እነዚህን ቅድመ ካንሰሮች ምርመራ ማድረግና ማከም ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህንንም በሚከተሉት መንዶች ይቻላል፡፡
1.የማህጸን ምርመራ (ሳይቶሎጂ፤ Pap Smear)
2.አሴቲክ አሲድ በመጠቀም የማህጸን የእይታ ምርመራ (VIA) ወይም የሉጉል አዮዲን (VILI)
3.የ HPV ዲ ኤን ኤ (DNA) ምርመራ:- የ HPV DNA ምርመራ ውድና የተሟላ ላብራቶሪን ስለሚፈልግ፤ በእኛ ሀገር ሌሎቹ አማራጮች በስፋት ከመገኘታቸውም በላይ አስተማማኝነታቸውም በብዙ ጥናቶች የተረጋገጡ ስለሆኑ እነሱን እንጠቀማለን፡፡

    የምርመራዎቹ አይነት እና የሚደረጉባቸዉ ጊዜያት

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚሳው ጥያቄ ታዲያ ሴቶች መቼ ነው እነዚህን ምርመራዎች ማድረግ መጀመር ያለባቸው የሚለው ነው፡፡ የቅርብ አለም አቀፍ የጤና መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ ዳግማይ መከላከል እንደሚከተለው መደረግ አለበት፡፡

👉እድሜ ከ 20 በታች
የዳግማይ መከላከል መርመራ አያስፈልግም
👉እድሜ 21-29
የማህጸን ምርመራ (Pap Smear, VIA or VILI) በየ 3 ዓመቱ፤
የ HPV DNA ምርመራ አያስፈልግም
👉አድሜ 30-65 የማህጸን ምርመራ (Pap Smear, VIA, or VILI) ) በየ 3 ዓመቱ፤ ወይም የማህጸን ምርመራ (Pap Smear, VIA, or VILI) +የ HPV DNA በየአምስት ዓመቱ
👉66 እና ከዚያ በላይ ያለፉት ሶስት የማህጸን ምርመራወች (Pap Smear, VIA or VILI) ወይም ሁለት የ HPV DNA ምመራወች በተከታታይ ኖርማል ከሆኑ የዳግማይ ምርመራ አያስፈልግም፡፡
አመሰግናለሁ
ዶ.ር አብዱ አደም 
የካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር

 

Leave a Reply