You are currently viewing የማህጸን በር ካንሰር ደረጃዎች እና ህክምና አማራጮች

የማህጸን በር ካንሰር ደረጃዎች እና ህክምና አማራጮች

            የማህጸን በር ካንሰር ደረጃ አሰያየም ስርዓት

የማህጸን በር ካንሰር ከ አንድ እስከ አራት ደረጃወች ሲኖሩት ደረጃወቹም የሚሰጡት ምርመራወች ከተደረጉ በኋላ ሲሆን ደረጃ ለመስጠትም TNM እና International Federation of Gynecology and Obstetrics (FIGO) የሚባል የአሰያየም ስርዓትን እንጠቀማለን፡፡

በብዛት ጥቅም ላይ የሚዉለዉን ባለ አራት ደረጃ አሰያየም ስርዓትን ስንመለከት

  1. ደረጃ አንድ የሚባለዉ፡- በካንሰር የተጠቁ ህዋሳት ወደዉስጠኛዉ የማህጸን በር ክፍል መጥለቃቸዉ እና ምናልባትም ወደ ማህጸን እና አቅራቢያ ወዳሉ የንፍፊት ጣቢያ (Lymph nodes) ሲሰራጩ ነዉ
  2. ደረጃ ሁለት የሚባለዉ፡- ካንሰሩ ከ ከማህጸን በር እና ማህጸን ሲያልፍ ነገር ግን የስረኛዉ የሴት ብልት ላይ ካልደረሰ ነዉ። ነገር ግን የካንሰር ህዋሳቱ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የንፍፊት ጣቢያ (Lymph Nodes) ሊዘልቁም ላይዘልቁም ይችላሉ።
  3. ደረጃ ሶስት የሚባለዉ፡-  ካንሰሩ የስረኛዉ የሴት ብልት ላይ ሲደርስ ነዉ። በዚህን ጊዜ ከፊኛ ሽንት የሚያስወጡትን ቱቦዎች (Ureters) ሊያግድ ይችላል። ነገር ግን የካንሰር ህዋሳቱ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የንፍፊት ጣቢያ (Lymph Nodes) ሊዘልቁም ላይዘልቁም ይችላሉ።
  4. ደረጃ አራት የሚባለዉ፡-  ካንሰሩ የሽንት ከረጢት (Bladder) ወይም የትልቁን አንጀት ክፍል (Rectum) በማጥቃት ከዳሌ ወጭ እያደገ ሲሆን ነዉ። ነገር ግን የካንሰር ህዋሳቱ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የንፍፊት ጣቢያ (Lymph Nodes) ሊዘልቁም ላይዘልቁም ይችላሉ። በዚህኛዉ ደረጃ ሲቆይ ወደ ሌሎች ሩቅ የሰዉነት ክፍሎች ለምሳሌ ወደ ጉበት፣ አጥንት እና ሳምባ ወደ መሳሰሉት ይሰራጫል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት አበዛኛወቹ ህመምተኞች በተለይም በታዳጊ ሀገራት የሚገኙቱ ወደ ህክምና ሲመጡ የህመሙ ደረጃ ከፍ ያለና (39% ደረጃ ሶስት፤ 17% ደረጃ አራት) ለማከምም አስቸጋሪ ከሆኑም በላይ የመዳን እድሉም ዝቅተኛ ሆኖ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሀገራችንን ጨምሮ በነዚህ ሀገራት ካንሰር የማይድን ህመም መስሎ የሚታየው፡፡

              የህክምና አማራጮች

የማህጸን በር ካንሰር እንደ ደረጃው
👉በቀዶ ህክምና፤
👉ጨረርና ኬሞቴራፒን አንድ ላይ በመስጠት፤
👉በጨረር ብቻ ወይም
👉በኬሞቴራፒ ብቻ ሊታከም ይችላል፡፡ የህክምናውን አይነት የሚወስነው ግን የህመሙ ደረጃና ሌሎች ሁኔታዎች ናቸው፡፡
የሚያሳዝነው እውነታ ግን ገና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ከፍተኛ የሆነ የባለሙያና የካንሰር ሀክምና ማእከላት እጥረት መኖሩ ብዙ መዳን የሚችሉ እናቶቻችንን በሞት ለማጣት አሰገድዶናል፡፡ ለምሳሌ ከ53 የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ 22ቱ ብቻ የጨረር ሀክምና መስጫ ሲኖራቸው ሀገራችን ደግሞ ይህ ጽሁፍ እስከተዘጋበት ቀን ድረስ አንድ የጨረር ህክምና ማዕከል አላት፡፡
ይህ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለሌሎችም ሴት እህትና እናቶቻችን እንዲደርስ ከስር ባሉት መተግበሪያዎች ሼር በማድረግ የድርሻችንን እናግዝ።
አመሰግናለሁ።
ዶ.ር አብዱ አደም
ረዳት ፕሮፌሰር እና የካንሰር ህክምና ስፔሺያሊስት

Leave a Reply