You are currently viewing የጨጓራ ካንሰር ምንነት

የጨጓራ ካንሰር ምንነት

ስለ ጨጓራ ካንሰር በደንብ ለመረዳት ያመቻችሁ ዘንድ ስለ ጨጓራ አወቃቀርና (Anatomy) ተግባራት በቅድሚያ መግለጹ መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ጨጓራ የ “J”ቅርጽ ያለውና ከምግብ መፍጫ ሥርዓት ውስጥ አንዱ ነው። መጠኑም ከሰው ወደ ሰው እንዲሁም ከምግብ እስከ ምግብ ይለያያል ምክኒያቱም በቀላሉ መለጠጥ ስለሚችል ነው፡፡ጨጓራ በዋናነት የሚከተሉት አምስት ክፍሎች አሉት (ስእልሁለትንተመልከቱ)
1.ካርዲያ (Cardia) – የመጀመሪያው ክፍል ሲሆን በጨጓራ ውስጥ ያለው ምግብ ተመልሶ ወደ ጉሮሮ እንዳይገባ ለመከላከል የሚያግዝ ቀጭን ጡንቻማ ክፍል ነው፡፡
2.ፈንደስ (Fundus) – በስተግራ እና ከ ከዲያፍራም በታች የሆነ ክብ ክፍል ነው ፡፡
3.ቦዲ (Body) – ትልቁ ክፍል ሲሆን ምግብ የሚደባለቀበት እና የሚፈጭበት ነው፡፡
4.አንትረም (Antrum) – ይህ ከፍል ደግሞ የተፈጨው ምግብ ወደ ትንሹ አንጀት ውስጥ ለመለቀቅ ዝግጁ እስኪሆን ድረስ የሚቆይበት ነው።
5.ፓይሎረስ(Pylorus) – ከትንሹ አንጀትጋር የሚያገናኝ ሲሆን የተፈጨውን ምግብ ወደ ትንሹ አንጀት የመጀመሪያ ክፍል(duodenum) ለማስገባት የሚያስችል ቫልቭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በተጨማሪም የትንሹ አንጀት ይዘቶች ወደ ጨጓራ እንዳይመለሱ ይከላከላል።

           አምስቱ የጨጓራ ግድግዳ ክፍሎች
የጨጓራ ግድግዳ የሚከተሉት አራት ሽፋኖች አሉት
1.የውስጠኛው ሽፋን (Mucosa) – ጨጓራባዶበሚሆንበት ጊዜ ጠባብና የተጨማደደ ገጽታ (rugae) ሲኖረው ጨጓራ በምግብ በሚሞላበት ጊዜ ደግሞ ይለጠጣል፡፡
2.ሁለተኛው ሽፋን (Submucosa) -ሰፋ ያለ የደም፤ የሊምፍ ፣ የነርቭ ሴሎችን እና ቃጫዎችን ከሚይዙ ህዋሳት የተሠራ ነው ፡፡
3.የጡንቻማ ሽፋን (Muscularis propria) – የጨጓራ ዋና ጡንቻ ሲሆን ከሶስት እርከኖች የተሠራ ነው ፡፡
4.የውጨኛው ሽፋን (Serosa) – የጨጓራውን ውጭ የሚሸፍን ከፍል ነው፡፡ 

       ጨጓራ የሚከተሉት ሶስት ዋና ዋና ስራዎች አሉት፡፡

1.ከጉሮሮ የመጣውን ምግብ በጊዜያዊነት ለ 2ሰዓታት ወይም ከዚያ በላይ ማከማቸት
2.ጡንቻዎቹን በማኮማተርና እና በማዝናናት ምግብን ማደባለቅ እና መፍጨት (Digestion)
3.የውስጠኛው ሽፋን ምግብን ለመፍጨት የሚያግዙ የሃይድሮክሎሪክአሲድ እና ኢንዛይሞችን የሚያመነጩ ልዩ ሕዋሳት እና ዕጢዎች አሉት። የምግብ መፈጨት ሂደቱ ሲያልቅ በፓይሎረስ በኩል አድርጎ ወደ ትንሹ አንጀት ይገባል፡፡

        የጨጓራ ካንሰር ምንነት

የጨጓራ ካንሰር ከ3000 አመታት ጀምሮ የታወቀ ሲሆን በጥንታዊ የግብጽ ሂሮግሊፊክ ጽሑፎች ላይ ይገኛል፡፡ የጨጓራ ካንሰር ከላይ ካየናቸው ክፍሎቹ ሁሉ ሊነሳ ቢችልም፤ እስከ 95% የሚሆነው የሚከሰተው ግን ከውስጠኛው ሽፋን ነው፡፡ የአለምየጤናድርጀትበቅርቡባወጣውዘገባመሰረትእ.ኤ.አ. በ 2018 ብቻ 1,033,701 አዳዲስየጨጓራካንሰርእና 782,685 ሞቶችበዚሁምክንያትተከስተዋል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የጨጓራ ካንሰር አምስተኛ (5.7%) የካንሰር ህመም እንዲሁም ሶስተኛው የሞት (8.2%) ምክንያት ነው፡፡
የጨጓራ ካንሰር በስርጭት ረገድ ጂኦግራፊያዊ ፣ ጎሳዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሰፊ ልዩነቶች ያሳያል፡፡ በዚህም እስከ 70% የሚሆነው የጨጓራ ካንሰር የሚከሰተው በድሀ ሀገሮች ነው፡፡ ባለፉት 60 ዓመታት በምዕራብ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ በሁለቱም ጾታዎች ላይ የጨጓራ ካንሰር ቀስ በቀስ ማሽቆልቆል አሳይቷል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ አጋላጭ የሚባሉ ሁኔታዎችን በመቀነሳቸውና ፍሪጅን በሰፊው በመጠቀማቸው ነው፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያም የጨጓራ ካንሰር በብዛት ከሚከሰቱት ካንሰሮች 13ኛው ሲሆን 10 ኛው የሞት መንስኤ ነው፡፡
ለሌሎችም እንዲደርስ ከስር ባሉት መተግበሪያዎች ሼር ያድርጉ።
አመሰግናለሁ
ዶ.ር አብዱ አደም
የካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር

Leave a Reply