You are currently viewing የማህጸን በር ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች እና አፈጣጠር ሂደቱ

የማህጸን በር ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች እና አፈጣጠር ሂደቱ

         የማህጸን በር ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች

የማህጸን በር ካንሰር ዋነኛው መንስኔ HPV (Human Papiloma Virus) በመባል የሚታወቅና በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፍ ቫይረስ ወይም የአባላዘር ህመም ሲሆን ከ90 በመቶ በላይ ለሚሆነው የማጸህን በር ካንሰር ምክንያት ነው፡፡ በርካታ የ HPV ቫይረስ ዝርያዎች ቢኖሩም፤ HPV 16 እና 18 እስከ 70 በመቶ በሚሆኑት ህመምተኞች ላይ ይታያሉ፡፡ ሌሎች አጋላጭ ሁኔታዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡፡
👉በለጋ እድሜ የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመር
👉ብዙ ልጆች መውለድ
👉ብዙ የወሲብ ጓደኞች መኖር (የሴቷ ወይም የወንዱ)
👉ሲጋራ ማጨስ
👉ውፍረት
👉የሰዉነት የበሽታ መከላከያ አቅም ማነስ (ለምሳሌ ከHIV ጋር የሚኖሩ ሰዎች)
👉ድህነት (ከዝቅተኛ ገቢ የተነሳ በሚመጣዉ የተመጣጠነ ምግብ ማጣት እና ንጽህና ጉድለት)
👉የወሊድ መከላከያን (የሚዋጠውን) ለረጅም ጊዜ መጠቀም (ከ5 ዓመት በላይ)
👉በቤተሰብ ዉስጥ በህመሙ የተያዘ ዘመድ መኖር ይካተቱበታል።

           የማህጸን በር ካንሰር ህመም አፈጣጠር ሂደት (Natural History)

የማህጸን በር ካንሰር ከመጀመሪያ ህመሙ ከመጀመሩ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስበት ሂደት በስፋት ከተጠኑ እና ከታወቁ ህመሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከላይ በተዘረዘሩትና ለህዩማን ፓፒሎማ ሳይረስ (HPV) ኢንፌክሽን የሚያጋልጡ ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም፡ የሰውነታችን መከላከያ አብዛኛውን ኢንፌክሽን ያሰወገደዋል፡፡ ነገር ግን የሰውነታችንን የበሽታ መከላከያ አቅምን መቋቋም የቻሉና ለረጅም ጊዜ የቆዩ የ HPV 16 እና 18 ኢንፌክሽን ለካንሰሩ መፈጠር ትልቁን ሚና ይጫወታሉ። በዚህም መሰረት የ HPV ኢንፌክሽን የማህጸን በር ካንሰርን ከአስር እሰከ ሰላሳ አመታት ቀድሞ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በሂደት ወደ ቅድመ ካንሰርና በመጨረሻም ወደ ካንሰርነት ይቀየራል፡፡ ስለዚህ የማህጸን በር ካንሰር እድሜያቸው ከ 30 አመት በታች በሆኑ ሴቶች ላይ የመከሰት እድሉ በጣም አናሳ ነው፡፡ ይህን ተፈጠሮአዊ ሂደት መረዳቱ ካንሰሩን በጥልቀት ለማወቅ ከማገዙም በላይ የቅድመ ካንሰር ምርመራን ጥቅም ለመረዳትና ህመሙ ወደ አሰከፊ ደረጃ ሳይደርስ ለመከላከልና ለመታከም ያስችላል፡፡

አመሰግናለሁ።
ዶ.ር አብዱ አደም
የካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር

Leave a Reply