You are currently viewing የማህጸን በር ካንሰር ምንድነዉ፣ ምልክቶቹስ?

የማህጸን በር ካንሰር ምንድነዉ፣ ምልክቶቹስ?

የማህጸን በር ካንሰር መከላከል የምንችለው ነገር ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ ደሃና በማደግ ላይ ያሉ ሃገራትን በብዛት የሚያጠቃ አያሌ ለሆኑ ሴቶች ሞት ምክንያት የሆነ የሴቶች የመራቢያ አካል ካንሰር ነው፡፡ ከላይ በስእሉ እንደሚታው ፤ የማጸህን በር ማለት የሴቶችን ማህጸን ከብልት ጋር የሚያገናኝ ክፍል ነዉ። ይህ የማህጸን በር ልጅ በሚወለድበት ወቅት የቀዳዳው መጠን በመጨመር ልጁ በቀላሉ ከማህጸን እንዲወጣ ያደርጋል፡፡የማህጸን በር ካንሰር ስንልም ከዚህ የአካል ክፍል የሚነሳናበአካባቢው ያሉትን የአካል ክፍሎች (ለምሳሌ ማህጸን፡ እንቁላል እጢ፡ አንጀት፡ የሽንት ፊኛ) ሲቆይ ደግሞ ሩቅ የሚባሉትን የአካል ክፍሎች (ለምሳሌ፡- ሳንባ፡ ጉበት፡ አጥንት) ድረስ ሊሰራጭ የሚችል የካንሰር አይነት ማለታችን ነው፡፡
በቅርቡ በወጣው የአለም ጤና ድርጅት (GLOBOCAN 2018) ሪፖርት እንደሚያሳየው ከሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በካንሰር አማካኝነት ለሚከሰቱት ሞቶች የማህጸን በር ካንሰር ከጡት ካንሰር በመቀጠል ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2018 ብቻ 569,847 አዳዲስ ታማሚዎች ሲመዘገቡ፤ ከነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት (311, 365(54.6%)) ህይወታቸውን በዚሁ ህመም የተነሳ አጥተዋል፡፡ በጠቅላላ ሲታይ ግን ባደጉት ሀገራት አዳዲስም ሆነ የሞት መጠኑ እጅጉን ቀንሶ አሁን ላይ አሳሳቢ ከሚባሉት የካንሰር አይነቶች እንኳን አናየውም፡፡ ለዚህም ምክንያቶቹ የተሟላ የቅድመ ካንሰር ምርመራ መኖር፤ የአጋላጭ ሁኔታዎች መቀነስ፤ የህክምና ቴክኖሎጂ መዘመንና ተደራሽነት መስፋፋት ናቸው፡፡ በአንጻሩ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት የአዳዲስ ታማሚችና የሞት መጠኑ በየአመቱ በ5% እየጨመረ ነው፡፡ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም የእድሜ ጣራ መጨመር፤ የቅድመ ካንሰር ምርመራና የህክመና ማዕከላት አለመስፋፋትና ውስንነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ከ80% በላይ አዳዲስ ታማሚዎች እንዲሁም ከ 88% በላይ ሞቶች የሚከሰቱት በነዚህ ሀገራት ነው፡፡ 
በጥቁር አንበሳ ሆሰፒታል የካንሰር ህክምና ክፍል ውስጥ በሚገኘው የአዲስ አበባ ካንሰር ሬጂስትሪ የቅርብ ሪፖርት መሰረትም የማህጸን በር ካንሰር (14.1%) ከጡት ካንሰር (31.5%) በመቀጠል ሁለተኛው በብዛት በሴቶች ላይ የሚከሰት ካንሰር ነው፡፡

     የማህጸን በር ካንሰር ምልክቶች

      የማህጸን በር ካንሰር ዋነኛው ምልክት ከማህጸን በር የሚፈስ ደም ሲሆን ይህም፡-
👉ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ፤
👉የወር አበባ መብዛት ወይም መዛባት፤
👉ከእርጣት በኋላ እንደገና ደም መፍሰስ መጀመር ሊሆን ይችላል፡፡
      ሌሎች ምልክቶች ደግሞ፡-
👉መጥፎ ሽታ ያለው ፈሳሽ ከማህጸን መውጣት፤
👉የሰጋራ መድርቅ፤ 
👉ደም የቀላቀለ ሽንት መሽናት፤
👉ክብደት መቀነስ፤
👉የጎን ውጋት እና እንደ ህመሙ ደረጃ ሌሎች ምልከቶች ሊታዩ ይችላሉ፡፡የካንሰሩን አይነት በትክክል ለመለየትና ደረጃውን ለማወቅ የአካል ምርመራ፤ የማህጸን ምርመራ፤ የደም መርመራ፤ የራጅና፤ የናሙናና ሌሎች ምመራዎች ያስፈልጋሉ፡፡
ይህ መልዕክት ለሌሎችም እንዲደርስ ከስር ባለዉ መተግበሪያዎች ለሌሎች ሼር ያድርጉ።

 

አመሰግናለሁ።
ዶ.ር አብዱ አደም
የካንሰር ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር

Leave a Reply