You are currently viewing በየዓመቱ 160 ሺህ ኢትዮጵያውያንን የሚያጠቃው ካንሰር

በየዓመቱ 160 ሺህ ኢትዮጵያውያንን የሚያጠቃው ካንሰር

የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ደረጃ መሠረት አንድ የካንሰር ሕክምና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ያለበት ለአንድ ሚሊዮን ሕዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ ሌሎች አገሮች ደግሞ በአንድ ማዕከል የሚያስተናግዷቸው የአገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እስከ አምስት ሚሊዮን ድረስ ማስኬድ ይችላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ቢያንስ ከ20 በላይ፣ ከተቻለ ደግሞ እስከ 100 የካንሰር ማዕከላት እንደሚያስፈልጓት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰርና የካንሰር ስፔሻሊስት አብዱ አደም (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

የካንሰር ሕክምና ማዕከል ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሕክምና ኮሌጁ በጊዜያዊ ማዕከል ውስጥ የካንሰር ሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስመልክቶ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር አብዱ በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ እስከ 160 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች በተለያዩ የካንሰር በሽታዎች ይጠቃሉ፡፡

ይህም በጤና ተቋማት የተመዘገበ እንጂ ወደ ጤና ተቋማት ሳይሄዱ የሚቀሩትን በየቤታቸው ያሉትን ጭምር ከታሰበ ቢታይ ቁጥሩ ከዚህ የበለጠ ከፍ ሊል እንደሚችል ከዶ/ር አብዱ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡  

በአደጉ አገሮች በየቀበሌው እያንዳንዱ የካንሰር ዓይነት እንደሚመዘገብ፣ ይህም የበሽታውን ሥርጭት እንዲታወቅ ማድረጉን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አገር አቀፍ የሆነ የካንሰር ምዝገባ እንደሌለ፣ ምዝገባውም ቢኖር በሆስፒታል ደረጃ ብቻ የተወሰነ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ምዝገባ የሚካሄደው በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል እንደሆነና ሆስፒታሉ ደግሞ የሚመመዘግበው የአገሪቱን ሳይሆን አዲስ አበባ ከተማን የካንሰር ሥርጭት ብቻ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ይኼንን በመገንዘብም ከጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል በተጨማሪ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ፣ በጎንደር፣ በጅማ፣ በሐዋሳ፣ በመቀሌና በሐሮማያ በድምር ስድስት የካንሰር ማዕከላትን በመገንባት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቸኛው አገልግሎት ሰጪ እንደመሆኑ መጠን በመላ አገሪቱ ያሉት የካንሰር ታካሚዎች ሪፈር ይደረጉበታል፡፡ ካለው ውስን አቅም አንፃር ሁሉንም በአግባቡ ለማስተናገድ ሆስፒታሉ ይቸገራል፡፡ ታማሚዎች የኬሞቴራፒ ለማግኘት ሁለትና ሦስት ወራት፣ የጨረር ሕክምና ለማግኘት ደግሞ ከአንድ ዓመት በላይ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕክምና ሳያገኙ ቀጠሮ በተራዘመ ቁጥር የሕመሙ ደረጃ እየጨመረ ወይም ከፍ እያለ የሚሄድበት ሁኔታም ሌላው አጣብቂኝ ነው፡፡ አንድ ታካሚ መጀመርያ በሕክምና ሲታይ የካንሰሩ ደረጃ አንድ ወይም ሁለት ከሆነበት፣ ተራውን በመጠበቅ ብቻ ካንሰሩ ወደ ደረጃ ሦስትና አራት የሚያድግበት አጋጣሚ እንዳለ ዶክተሩ ይገልጻሉ፡፡

ለካንሰር ሕመም ከሚዳርጉ ከመንስዔዎቹም መካከል አንዱ የኅብረተሰቡ የአኗኗርና የአመጋገብ ሁኔታ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል የካንሰር ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉ ሰዎች ብዙ አልነበሩም፡፡ ከጊዜ በኋላ በርካቶች ካንሰር ላይ ያላቸው ግንዛቤያቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ቅድመ ካንሰር ምርመራ የማድረግና ካንሰርን ለመመርመር የሚያስችሉ መሣሪያዎች በሦስተኛው ዓለም ውስጥ እየተስፋፉ እንደመጡ፣ ከዚህ በፊት ሳይታወቁ የቀሩ ሕመሞችን በቀላሉ በምርመራ ማወቅ እንደተቻለ፣ ይህም ቁጥሩ እየጨመረ ለመምጣቱ ምክንያት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

እንደ ዶ/ር አብዱ ማብራሪያ፣ ካንሰር በማናቸውም ዕድሜ ክልል በወንዶችም በሴቶችም ይከሰታል፡፡ በአገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የሴቶች ሁኔታ ሲታይ የጡት ካንሰር የመጀመርያውን ደረጃ ይይዛል፡፡ በተለይ በአገራችን 33 በመቶ የሚሆነው የጡት ካንሰር ሲሆን፣ ከዚያ በመቀጠል የማኅፀን በር ካንሰር በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ በወንዶች በኩል ደግሞ ያለው ሁኔታ ሲታይ ፕሮስቴት ካንሰር የመጀመርያ ደረጃ ሲሆን፣ የሳምባ ካንሰርም በወንዶችና በሴቶች በብዛት ይታያል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን የሳምባ ካንሰር አደገኛ እንደሆነ፣ በፊት ሴቶች ትምባሆ የማጨስ ልምዳቸው ትንሽ እንደነበር፣ አሁን ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴት አጫሾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን፣ በዚያው መጠንም በሳምባ ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው እየጨመረ እንደመጣ ተናግረዋል፡፡  

‹‹የሠለጠነ የሰው ኃይልን በተመለከተ በአገሪቱ ያለው ትልቁ ችግር በሰው ሀብት በኩል ያለው እጥረት ነው፡፡ በዚህ ሕክምና ኮሌጅ ያለው የካንሰር ስፔሻሊት እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለል ተብሎ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል በካንሰር ሕክምና ስፔሻሊቶችን እያስተማረ ነው ያለው፡፡ አቀባበሉ ግን በጣም ውስን ነው፡፡ ይህም ማለት በዓመት አሥር የካንሰር ስፔሻሊስቶችን ነው እየተቀበለ ያለው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ያለው የካንሰር ስፔሻሊስቶች ቁጥር 13 ብቻ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ እያስገነባ ያለው የካንሰር ሕክምና ማዕከል ሲጠናቀቅ 150 እና ከዚያ በላይ አልጋ የሚኖሩት ሲሆን፣ ሁሉንም ዓይነት የካንሰር ዓይነቶችን ሕክምና እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱም የልህቀት ማዕከልና ለሁሉም ማዕከላት እንደ ሪፈራል ማዕከል ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችል፣ ለዚህም አምስት የጨረር ማሽኖች ይኖሩታል፡፡

ከሚሰጣቸውም የሕክምና አገልግሎቶች መካከል የመቅኒ (ቦንማሮ) ንቅለ ተከላ፣ የቀዶ ሕክምና (ለዚህም የሚሆኑ ወደ ስድስት የሚጠጉ የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ይኖሩታል) የደምና የማኅፀን ካንሰሮች ይገኙበታል፡፡

 ይህን ሁሉ አገልግሎት ለመስጠት በቂ የሰው ኃይል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የሚያግዝ ትምህርት ወይም ሥልጠና ለመስጠት ታቅዷል፡፡ የትምህርት ፍኖተ ካርታም እየተዘጋጀ ሲሆን፣ ዝግጅቱም እየተከናወነ ያለው የውጭ አገር ተሞክሮዎችን በመቅሰም ነው፡፡

‹‹እስካሁን ድረስ በስፔሻሊስት ያለውን ሥልጠና የምንከታተለው በአገራችን ባለው ሪሶርስ ወይም በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻሊስት ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና የተመለመሉ ዘጠኝ ስፔሻሊስቶች በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመማር ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ስድስቱ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ዓመት የደረሱ ሲሆን፣ ሌሎቹ ሦስቱ ደግሞ ዘንድሮ የሚገቡ ናቸው፡፡ ይህም በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከ20 እና ከዚያም በላይ ነው የምንፈልገው፤›› ብለዋል፡፡

የስፔሻላይዜሽን ሥልጠናን በተመለከተ ያለው ችግር ከፍተኛ የሆነ የስፔሻላይዜሽን ጥያቄ ላለባቸው ማዕከላት ቅድሚያ አለመስጠት ነው፡፡ ይህም ማለት ቅበላው ለሁሉም ሆስፒታሎች በሚሆን መልኩ ውጤት ብቻ በማየት ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ቀርቶ የስፔሻላይዜሽን ሥልጠና ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ለካንሰር ሕክምና ማዕከላት መሆን እንዳለበት ነው ዶ/ር አብዱ የተናገሩት፡፡

ከሐኪሞች በተጨማሪ የጨረር ማሽኖችን የሚቆጣጠሩ ሜዲካል ፊዚሺስቶች  እንደሚያስፈልጉ፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው አንድ ፊዚሺስት ብቻ እንደሆነ፣ ለእያንዳንዱ ማሽን ቢያንስ ሁለት እንደሚያስፈልጉ ሜዲካል ፊዚስት ትምህርት የሚሰጠው በማስተርስ ዲግሪ መርሐ ግብር እንዲሆንና ይህ ዓይነቱ ትምህርት ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ እንደሌለ ዶ/ር አብዱ አስታውቀዋል፡፡

በሚቀጥለው ሦስት ዓመት ውስጥ የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ እስከዛው ድረስ የሰው ሀብትን ለማሟላትና ልዩ ልዩ የሕክምና መሣሪያዎችን ለማደራጀት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ እንደ ዶ/ር አብዱ ገለጻ፣ በጊዜያዊ ማዕከሉ ውስጥ እየተሰጠ ያለው ተመላላሽ የካንሰር ሕክምና የተጀመረው ባለፈው ወር ነው፡፡ ሕክምናውንም እያገኙ ያሉት እዚሁ ሆስፒታል ተመርምረው ልዩ ልዩ ዓይነት የካንሰር በሽታ ያሉባቸውን ታካሚዎች ብቻ ናቸው፡፡ ጊዜያዊ ማዕከሉ ወደ 14 የሚጠጉ ጠቅላላ ሐኪሞችና 14 ነርሶች አሉት፡፡  

ሲስተር ትዝታ በለው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የኦንኮሎጂ ክፍል የነርሶች ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፣ ጊዜያዊ ማዕከሉ በቀን ለ20 የካንሰር ታካሚዎች ተመላላሽ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ ይኼንንም አገልግሎት ለማግኘት ከሚመጡት ታካሚዎች መካከል እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት የጡት፣ የአንጀት፣ የጨጓራና በአጠቃላይ የሆድ ዕቃ ካንሰር ያደረባቸው ናቸው፡፡

ጊዜያዊ ማዕከሉ ኬሞቴራፒ የሚሰጥባቸው ሰባት አልጋዎች እንዳሉት፣ ኬሞቴራፒ ሕክምና ጥቅሙ ደግሞ ሴሎችን በመግደል ላይ ያተኮረ የካንሰር ሕክምና እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ምልክቶቹ ቶሎ ስለማይታዩ ብዙ ታካሚዎች ለሕክምና የሚመጡት የካንሰሩ ደረጃ ከፍ ካለ በኋላ መሆኑንና ለዚህም መፍትሔው ኅብረተሰቡ በየጊዜው ጠቅላላ የሕክምና ምርመራ ማድረግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

በታደሠ ገብረማሪያም፣ ለሪፖርተር የተሰጠ ቃለ መጠይቅ።
መስከረም 2011 ዓ.ም

Leave a Reply